...

ኢትዮጵያ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንቅስቃሴዎቿን የቃኘው የምክክር መድረክ

ከትናንት አንስቶ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም ሮቦቲክስ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በዛሬው መድረክም የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ገለፃዎች የቀረቡ ሲሆን እነርሱን መነሻ በማድረግም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡት ውስጥ ቀዳሚ የነበረው ከአይኮግ ላብስ የመጡት አቶ ህሩይ ፀጋዬ “Beware of Greeks Baring Gifts: Robotics in Ethiopia” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ሮቦቲክስ ላይ ያተኮረ ገለፃ ነው፡፡ በገለፃቸው ስለ ሮቦቶች ምንነት፣ ከቀድሞ ጊዜያት አንስቶ የነበረ አረዳድን እንዲሁም ሀገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ድክመት እና ዕድል አብራርተዋል፡፡ ሮቦቲክስን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ዕንቅስቃሴዎች እጅግ ውስን ከመሆናቸውም ባሻገር የተሰሩ አነስተኛ ስራዎችም በኢንዱስትሪው ሊሰጣቸው ከሚገባው ቦታ በላይ ተጋኖ እንደሚወራላቸው የተናገሩት አቶ ህሩይ ዘርፉን ለማሳደግ የትምህርት ተቋማትና እና ባለድርሻዎች ተገቢውን ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተቋማቸው አይኮግ ላብ ውስጥ የተኬዱ ርቀቶችን እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንም ለታዳሚው በምሳሌነት አቅርበዋል፡፡

የዕለቱን ሁለተኛ ገለፃ ያቀረቡት በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ውስጥ በተመራማሪነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ቃልኪዳነ ገዛኸኝ ሲሆኑ እርሳቸውም በበኩላቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ኢ-ኮሜርስ ግንኙነት ላይ በማተኮር ዳሰሳቸውን አጋርተዋል፡፡ በገለፃቸው የኢ-ኮሜርስ አይነት ታሪክ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሊጫወትበት ስለሚችለው ሚና ከመጥቀስም ባሻገር በኢትዮጵያ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ይችላሉ ያሏቸው የቴክኖሎጂው ገፅታዎችን አስቃኝተዋል፡፡ በአሁን ሰዓት 14 ያህል ኢ-ኮሜርስ ላይ አተኩረው የሚንቀሳቀሱ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ያሉት አቶ ቃልኪዳን በሀገራችን በቅርቡ እያቆጠቆጠ ላለው የኢ-ኮሜርስ እንቅስቃሴ የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ተከትሎ የመጣውን አካላዊ ግንኙነትን የመቀነስ ፍላጎትን ጨምሮ በጎ ዕድልን ፈጥረዋል ያሏቸውን ነጥቦች አስቀምጠዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ አይሲቲ ፓርክ፣ ሮቦ ሮቦቲክስ፣ መረጃና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ ኢትዮ-ቴኬኮምን ጨምሮ ከግልና መንግስት መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የትምሀርት ተቋማት የተወከሉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡Post Comments(0)

Leave a reply