...

የእንሰት ምርትን በዘመናዊ መንገድ ማልማት

የእንሰት ተክል አትዮጵያ ውስጥ በብዛት ከሚበቅሉ እና በተፈጥሮ ከታደልንባቸው ውድ ስጦታች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከ 20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች መሠረታዊ ምግብ የሆነው ይህ ተክል በብዙ አካባቢዎች ጥያቄ ሆኖ የቀረውን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚገለፁት እንሰትን ለማምረት በሚተገበረው ሂደት ትክክለኛ አሰራር ባለመኖሩ እና የአጠቃቀም ስርዓቱ ችግር የማያጣው በመሆኑ ከ24 እስከ 25 በመቶው የእንሰት ምርት ለብክነት የተዳረገ ይሆናል፡፡ ይህ ትልቅ ሃብት የተለያዩ የቴክኖሎጂ አመራጮች እና የአሰራር ስርዓቶች ተግባራዊ የሚደረግብት ከሆነ በአፍሪካ ቀጣናዎችም ይሁን በአለም ገበያ እጀግ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም አለው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች በአከባቢው እና በሌሎች አጎራባች ቦታዎች ለማጥናት እንደሞከሩት እንሰት የሚቀነባበርበት ሁኔታ እና የማጓጓዣ መንገዶቹ ለምርት ብክነት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል ሲሆኑ ከዚህ ተጨማሪ እንሰቱን ከመቁረጥ እስከ ማብላላት ያለው ሂደትም በባህላዊ መንገድ የሚከናወን በመሆኑ በተለይም የሴቶችን ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ የሚጠይቅ፣ ለድካምና ለተለያዩ ህመሞች የሚያጋልጥ እንዲሁም የምርት ጥራት ችግርና ብክነት የሚያስከትል ነው፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ እና ሂደቱን በፈጠራ ለመደገፍ የእንሰት መቁረጫ፣ መፋቂያ፣ መፍጫና መጭመቂያ ማሽኖቹ በዩኒቨርሲቲው ሜካኒካል ወርክሾፕ የተሠሩ ሲሆን በሌሎች ሀገራት ጥቅል ጎመንን ለማብላላት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ በማምጣት ለእንሰት ማብላያና ማስቀመጫነት እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ማስቀመጫዎቹን በአካባቢው በቀላሉ በሚገኙ የሸክላና ፕላስቲክ ቁሳቁሶች ለመተካትም እየተሠራ ሲሆን ይህም በዘመናዊ መንገድ የእንሰት ምርትን ይበልጥ ለማሳደግ እና ለማልማት በእጅጉ ያግዛል፡፡

የእንሰት ምርትን በባዮቴክኖሎጂ እና የዘረ መል ምህንድስና ለውጥ በመጠቀም ይበለጥ ማሳደግ እንደሚቻል የሚያስረዱ ቢኖሩም ከዚያ በፊት ግን ያሉንን አገር በቀል እውቀቶች ዘመናዊ ከሆኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማጣመር የራሳችንን የውስጥ አቅም ማሳደግና ቅድመ ጥንቃቄዎች ላይ ማተኮር መልካም ነው የሚሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ ከበሽታ ነፃ የሆኑ በርካታ ችግኞችን በአጭር ጊዜ ለማፍላት በሚያስችለው እንደ ቲሹ ካልቸር (Tissue Culture) ያለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የእንሰት ምርትን ይበልጥ ማሳደግ ይቻላል፡፡ የእንሰት ተክል በባህላዊውም አሠራር ለማባዛት የማያስቸግር፣ ከአንድ ተክል ከ100 እስከ 200 ወይም ከዚያ በላይ ችግኞችን ማግኘት የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ዘዴም በቂ ችግኞችን በቀላሉ አፍልቶ ማሠራጨት እንሚቻል ይጠቀሳል፡፡

በሌላም በኩል የአፈር ለምነትን ለማዳበር የሚረዱ ተፈጥሯዊ የሆኑ ዘዴዎችን፣ እንዲሁም ከእንሰት ጋር በተጓዳኝ ሊለሙ የሚችሉ የሰብል ዓይነቶችን በማስፋፋት የብዝሃ ሕይወት ሀብት ስብጥሩን ማብዛት ላይ ትኩረት በመስጠት ምርታማነትን ማሳደግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የእንሰት አመራረት በተለያየ ወቅት ምርት ለማግኘት ከማስቻሉ ባሻገር ከሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥና ያንንም ተከትለው የሚመጡ ተግዳሮቶችንም በተሻለ ተቋቁሞ ለማለፍ የሚችል ተክል በመሆኑ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ የእርሻ ስርዓት (Diversity Based Farming) በመተግበር ዘርፉን ይበልጥ ማበረታታትና ማሳደግ ይቻላል፡፡

ምንጭ፡ The Ethiopian Herald እና Arba Minch UniversityPost Comments(0)

Leave a reply